#EthioMuslims በእፎይታ ጊዜው የትግላችንን - TopicsExpress



          

#EthioMuslims በእፎይታ ጊዜው የትግላችንን እድገት እናረጋግጥበታለን! ረቡእ ነሐሴ 8/2005 ሃገር አቀፉ የዒድ ዕለት ተቃውሞ መርሃ ግብር ይፋ በሆነበት ወቅት አንድ ወሳኝ መልዕክትም አብሮ ተላልፎ ነበር፡፡ ይኸው መልዕክት እንዲህ የሚል ነበር፡- ‹‹በዚህ የኢድ ተቃውሟችን ለሌላ ተጨማሪ ጊዜ ለመንግስት እና ለሚመለከተው አካላት መልእክታችንን በማድረስ የመንግስትን ተግባራዊ ምላሽ ለመጠበቅ ስንል የጁምአ ተቃውሞዎችን ላልተወሰኑ ጊዜያት የምናካሂድ አይሆንም፡፡ በተለይም በመስከረም 27 የተካሄደው የመጅሊስ የቀበሌ ሹመት በእለቱ ተምሳሌታዊ ስርአተ ቀብር ስለሚፈጸምለት ይህ ነው ተብሎ የሚወጣ አካል ባለመኖሩ መንግስት የጥሞና ጊዜ ወስዶ ሕዝብ ለተጠየቃቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሹን እንዲሰጥ የጁምአ ተቃውሞዎች ላልተወሰኑ ጊዜያት ይቆማሉ፡፡›› ይህ መልእክት መንግስት የመብት ጥያቄያችንን አጉል በመፈረጅና እኛ ላይ ከባድ አፈና እያደረገ በሚገኝበት ወቅት መተላለፉ ህዝበ ሙስሊሙ የሚያካሂደው የመብት ትግል እጅግ ሰላማዊና መፍትሄ ለማግኘት የሚጓዝ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፤ በዒድ ተቃውሞ እለት በሃገር አቀፍ ደረጃ ፆታና እድሜ ሳይለይ የደረሰብን ጥቃት መላውን ህዝብ ‹‹ይህ ለምን ሆነ?›› ብሎ እንዲጠይቅ አስገደደው እንጂ፡፡ በዒዳችን በዓል ሙስሊሙ ላይ የደረሰው ጥቃት መብትን የመጠየቅ እና ያለመጠየቅ፣ ተቃውሞ የማሰማት እና ያለማሰማት፣ ሰላማዊ የመሆን እና ያለመሆን ጉዳይ ፈፅሞ አልነበረም፡፡ የጥቃቱ ሰለባ ለመሆን ቅድመ ሁኔታው የዒድ ሰላት ሰግዶ የሚመለስ ሰው ብቻ መሆን በቂ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ለሙስሊሞች ሰጥቻለሁ እያለ ከሚመጻደቅበት መብት አንዷ የምትባለውን በአመት ሁለት ዒዶችን ተሰብስቦ መስገድን በሚዲያ እየጠሩ በዱላ እና በአፈሙዝ ከመከልከል አይተናነስም፡፡ በዚህም መንግስት የከፈተው ዘመቻ ማንንም ከማንም የማይለይና መደብደብና መገደልም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እጣፈንታ መሆኑ አይተናል፡፡ ግን መብትን እየጠየቁ መጠቃት የበለጠ እልህ የሚፈጥርና ወኔን የሚያጎመራ በመሆኑ ይበልጥ የሚያበረታን ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ መንግስት ሰላማዊ ትግላችንን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ያሳየናቸውን ሰላማዊ አካሄዶች እና የፈጠርናቸውን የመውጫ ቀዳዳዎች በአግባቡ እንዳልተጠቀመባቸው ደጋግመን አይተናል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአምናው ዒደል ፊጥር ግዙፍ ህዝባዊ ተቃውሞ መላው ኢትዮጵያውያን የጥያቄዎቻችንን ሕጋዊነት እና ሕዝባዊነት በአይናቸው ያዩበት ወቅት ነበር፡፡ መንግስት ጥያቄውን ያቀረበው መላው ህዝብ መሆኑን ለኢቲቪ ግብአት መውሰድ እስኪቸገር ድረስ በተግባር መሰከረ፤ ህዝቡ ጥያቄውን ለማድረስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄውን ለማስመለስም እንደማይሳነው ህዝባዊ አቅሙን እና ወኔውን በውል ተረዳ፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት ማግስት የታወጀውን የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን ሞት ታሳቢ በማድረግ ላልተወሰኑ ጊዜያት ተቃውሞው ጋብ እንዲል ተደርጎ ነበር፡፡ ይህንን ተግባራዊ እርምጃ ግን መንግስት ለሃገራዊ መግባባትና መረጋጋት ከመጠቀም ይልቅ መሪዎቻችንን ይበልጥ በማሰቃየት፣ ህዝባችንንም እያሳደደ በማሰር ነበር መልስ የሰጠው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ለጥያቄዎቹ መልስ ያስገኛሉ የሚባሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ ለመጠቀም በሩን ክፍት አድርጎ ቢጓዝም የመንግስት ግብታዊነት ግን የህዝቡ ጥረት እንዲመክን አድርጎታል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ እነሆ ከአንድ አመት በኋላ ግዙፍ ህዝባዊ መነቃቃት ባለበት ሰአት እና የመንግስት ፕሮፖጋንዳዎች ሙሉ በሙሉ ከሽፈው ከአዘጋጆቹ ሌላ አድማጭ ባጡበት ሰአት እራሱን አንድ ደረጃ ወደኋላ ለመግታት የወሰነው ገና የዒድ ተቃውሞ ከመደረጉ በፊት ነበር፡፡ ይህ ተቃውሞውን ላልተወሰነ ግዜ የማቆም ሃሳብ ከተወሰነበት ግዜ አንስቶ በርካታ ቅሬታዎችን ቢያስነሳም ብዙሃኑ ህዝበ ሙስሊም ግን ለሃገራዊ ሰላም እና ለትግላችን አቅጣጫ መጠበቅ ሲል በፀጋ ተቀብሎት ነበር፡፡ እናም ወደ ዒድ ተቃውሞ ሲሄድ ‹‹ዛሬ አመት ከመንፈቅ ያቀረብኳቸውን ጥያቄዎች በሚሊዮኖች ድምፅ አጅቤ ዳግም አቀርባለሁ፡፡ መንግስትም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ጥያቄዎቼን ቆም ብሎ እንዲያጤነው ተገቢውን ግዜ ለመስጠት ከዒድ በኋላ የእፎይታ ግዜ እሰጣለሁ›› የሚል ፍፁም ሰላማዊ እና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ውሳኔን አስቀድሞ ነው ወደ ዒዱ ተቃውሞ የተመመው፡፡ ከስኬታማው የዒድ ተቃውሞ መልስ የገጠመው ኢ-ህገመንግስታዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ ግፍ ግን መቼም የማይረሳ ነበር፡፡ ግና ህዝበ ሙስሊሙ ከበደል የነፃ ጉዞ አድርጎ አያውቅም፤ የመንግስትን ሃላፊነት የጎደለው ኣካሄድም የሚያውቀው ገና ከጥያቄዎቻችን ጅማሮና በመሪዎቻችን ላይ ከተወሰደው እርምጃ አንስቶ ነበር፡፡ ህዝብ ቃሉንና መርሁን የሚጠብቀው በመንግስት አካሄድ ላይ ተመስርቶ ባለመሆኑ ዛሬም ከመንግስት ግብታዊ አካሄድ እና ኢ-መንግስታዊ ባህሪ ማግስት ባሰብነው መልኩ የእፎይታ ጊዜውን አፅንተነዋል፡፡ ይህም መንግስት በነፈሰበት የማንነፍስ፣ ሽብር ሲነዛ በሽብር የማንናጥ መሆናችንን እየሳየንበት ነው፡፡ አሁን ከሚታዩና ወደፊት ከሚኖሩ ሁኔታዎች አኳያ የእፎይታ ጊዜውን የመከለስ እድል ቢኖረውም በእፎይታ ግዜው ውስጥ ታሳቢ የተደረጉ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በእፎይታ ግዜው አሁንም እየተደበደብን ለሰላም ያለንን ተገዥነት በተግባር እናሳይበታለን፤ መንግስት እረፍት የለሽ የህግ ጥሰት እና የሰብአዊ መብት ገፈፋ እያደረገም እኛ ደግሞ የኢስላማዊ ትዕግስትን ምንነት እናሳይበታለን፡፡ በሂደቱም እየተመነዳን እንማርበታለን፤ ጉዳዩን መላው ኢትዮጵያዊ በሚገባ እንዲያጤነውና ለሃገር በሚበጅ መልኩ እልባት እንዲያገኝ ሃገራዊ ሃላፊነታችንን እወጣበታለን፡፡ ይህ የእፎይታ ግዜው አንዱ አላማ ነው፡፡ ሌላው በዒድ ተቃውሞ እለት የተካሄደውን የመስከረም 27 የመጅሊስ የቀበሌ ሹመትን አስመልክቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምናደርግበት ወቅትም ይሆናል፡፡ ይህ ግብአተ መሬቱ የተፈፀመለትን ግኡዝ ሹመት ምንነት በተጨባጭ ለማሳየት፣ መርሃ ግብሮችን ነድፈን የሚታይ ስራ ለመስራት የእፎይታ ግዜውን እንደመልካም አጋጣሚ እንጠቀመዋለን፡፡ ከዚህም ባለፈ የእፎይታ ግዜው ለትግላችን ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተዘዋዋሪ አማራጮችን ለማስቀጠልና አዳዲስ መንገዶችንም ለማስጀመር ታሳቢ አድርጓል፡፡ አምና ከነበረን ግዙፍ ህዝባዊ ወኔ ሳንቀንስ የመንግስት በደል የጨመረልን ተጨማሪ ቁጭት ጋርም ለመርህ እና ለአቋም የምንገዛ መሆናችንን በማሳየት ሰላማዊ ትግላችንን እንደከዚህ ቀደሙ ማስፋፋት እና ማርገብ የትግል ስልት እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ በተግባር የምናሳይበት ነው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ የምንገመግምበትና ስለሂደታችን የህዝብ ለህዝብ ውይይቶች የምናደርግበት ወቅት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ የእፎይታ ግዜ በመሆኑም ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና! አላሁ አክበር! Like ☑ Comment ☑ Share ☑ ይሄን ሊንክ ጠቅ አድርገው ይከተሉና አዲሱ ገጻችንን ላይክ ያድረጉ! https://facebook/DimtsachinYisema2
Posted on: Wed, 14 Aug 2013 13:36:10 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015