#Ethiopia #EthioMuslims #DY #EthioMuslimsPrisoners በክልሎች - TopicsExpress



          

#Ethiopia #EthioMuslims #DY #EthioMuslimsPrisoners በክልሎች ያሉ ታሳሪዎችን ፍትህ እንጂ ህዝብ አልረሳቸውም! ሐሙስ ሐምሌ 25/2005 ሰላማዊ ትግል ሰላማዊነቱ የሚገለፀው በሌሎች ላይ ሁከት እና ብጥብጥ ባለማንሳት እና ለሌሎች ስጋት ባለመሆን እንጂ ታጋዩ ላይ ሁከት እና ስጋት ሳይፈጸምበት የሚያልፍበት ጊዜ እምብዛም አይታይም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ታላቅ ሰላማዊ ትግል እያደረግን እንገኛለን፡፡ የእኛ ሰላማዊነት ሁከት የሚያስቡ እና በስጋት ሊያስቆሙን ለሚያስቡ አካላት ምንም ቀዳዳ ባይኖረውም ህግ አላፊዎችን ግን ያሻቸውን ከመፈፀም አላገዳቸውም፡፡ የዚህ ትልቁ ማሳያ ደግሞ በክልሎች እየተፈፀመ የሚገኘው ዘግናኝ በደል እና የፍትህ መጣስ ነው፡፡ መንግስት በክልሎች ለሚሰነዝረው ጥቃት የማስመሰያ ምክንያት እንኳን ማቅረብም አላስፈለገውም፡፡ ሙስሊሞችን ወደ እስር ለመወርወርም እንደ ሁልጊዜው ህገ መንግስታዊ ሂደቶች በጭራሽ ታሳቢ አልተደረጉም፡፡ በክልሎች የሚገኙ ታሳሪዎች በውድቅት ሌሊት ከተኙበት ታፍነው፣ አልያም መስጂድ ሲገቡና ሲወጡ፣ ካልሆነም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲጨዋወቱ በአፈሙዝ ተገደው ይወሰዳሉ፤ የት እንደሚወሰዱ መጠየቅ ደግሞ በወቅታችን የማይታሰብ ሆኗል! ስለሚፈፀምባቸው የህግና ሰብአዊ መብት ጥሰት ማንሳት ከቅብጠት ተቆጥሯል፡፡ በዚህ መልኩ ከሰላማዊ ትግላችን ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወደ ማዕከላዊው የግፍ ማዕከል እየመጡ ብርቅዬ መሪዎቻችን ያሳለፏቸውን ጥቁር ቀናት ያሳልፋሉ፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት በየክልል ዋና ከተማ እና የዞን ከተማዎች ፍትህ ፊቷን አዙራባቸው የኢትዮጵያዊነትን ትርጉም በሚያዛባ ይዞታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከነሱ የሚበልጡት ደግሞ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ታጉረው በስካር የነበዙ መርማሪዎች የሌሊት የዱላ ጥም ማርኪያ እና ያደረ ቂም መወጫ ሆነዋል፡፡ የሴቶች፣ የህፃናት እና የአረጋውያን አለም አቀፍ ልዩ መብቶች በልዩ በደሎች ተቀይረው ሴቶች አያያዙ እጅግ በከፋ እስር ቤት ወልደው ከልጆቻቸው ጋር የበሽታ ተጋላጭ እየሆኑ፣ አረጋውያን ከእንጨት በተሰሩ አግዳሚዎች ለቀናት በረንዳ ላይ እያደሩ ነው፡፡ ለነዚህ ወንድምና እህቶች ህጉ በሚያዘው መልኩ ፍርድ ቤት መቅረብ እና በክስ ሂደት ውስጥ የህልም እንጀራ ሆኖባቸዋል፡፡ ከሰላማዊ ትግላችን ጅማሮ አንስቶ እስከ አሁኑ ሰአት ድረስ በክልሎች የሚፈፀሙ ግፎችን መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በተናጠል ያውቃቸዋል፡፡ የታሳሪዎች ስም፣ ቁጥር እና የሚፈፀምባቸው የበደል አይነት በዝርዝር ይታወቃል፡፡ በአቅም እና በመረጃ መለዋወጫ አማራጭ እጥረት ምክንያት ተገቢውን ትኩረት ያላገኙ ቢመስልም መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ስለነርሱ እንቅልፍ እያጣ ነው፡፡ እኛም ስለወኪሎቻችን የእስር ስቃይ እና ህገወጥ የፍርድ ሂደት ስናወራ በመላው ሃገሪቱ ያሉ ታሳሪዎች ስቃይ ከነሱ ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ በሚገባ እናውቃለን፡፡ አዎን! በመላው ሃገሪቱ የእምነት መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ፍትህ የተነፈጉ ሁሉ የሰላማዊ ትግላችን ማጠንጠኛ ናቸው፡፡ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ›› ስንል የምንጮኸውም ኢቴቪ እንደሚያዛባው ኮሚቴዎቻችንን ብቻ ማለታችን ሳይሆን እነዚህን በሺዎች የሚቆጠሩ ፍትህ ጀርባዋን ያዞረችባቸውን ተበዳዮች ጭምር ነው፡፡ ኮሚቴዎቻችንን በአስር ሺዎች ሆነን ቃሊቲ ስንዘይራቸው እነርሱ ለሚሰቃዩለት ዓላማ ተመሳሳዩን መስዋእትነት የሚከፍሉትን ሺዎችን እየዘየርን ነበር፡፡ የኮሚቴዎቻችንን ህገወጥ የፍርድ ቤት ተውኔት ስናጋልጥና ‹‹ፍትህ ሆይ የት ነው ያለሽው?›› ብለን ስንጠይቅ የሺዎችን ፍትህ ንፍገት መልሰን እያስተጋባን ነው፡፡ ‹‹ሳይፈቱ ሰላም የለም!›› ማለታችን መንግስት መጫወቻ ካርድ አድርጎ የያዛቸውን ኮሚቴዎቻችንን ብቻ ሳይሆን በመላው ሃገሪቱ ስለ ሰላማዊ ትግላችን ሲሉ ለህገወጥ እስር የተዳረጉትን በሙሉ ማለታችን ነው፡፡ ይህም የትግላችን ሃገራዊነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አክራሪነትን በመዋጋት ሽፋን ኢላማ የተደረጉት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ጤናማ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች እና የአምልኮ ነፃነቶቻችን ናቸው፡፡ በመሆኑም ጥያቄዎቻችን ሃገራዊ ጥያቄ ናቸው፤ ኮሚቴዎቻችንን ስንወክል በሃገር አቀፍ ደረጃ ባሰባሰብነው የውክልና ፊርማ ነውና፡፡ የሂደታችን ሰላማዊነት ሃገር አቀፍ ነው፡፡ በሰደቃና አንድነት ፕሮግራሞች የተነቃነቀው መላው ህዝባችን ነው፡፡ እንዲሁም እየተጎነጨነው ያለነው የግፍ ፅዋ ቦታ ሳይለይ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚፈፀምብን የህግ ጥሰት ነው፡፡ የትግላችን መቋጫም እንደሃገር የተደቀነብን እስልምናን እና ሙስሊሞችን የማጥቃት ዘመቻ እና ለእሱ መፈጠር ምክንያት የሆኑ የመንግስት የተዛቡ አመለካከቶች መስተካከል ነው፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ በመላው ሃገሪቱ በሙስሊሞች ላይ እየተፈፀመ ስላለው የእምነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት እንጮሃለን፡፡ አላሁ አክበር! Like ☑ Comment ☑ Share ☑ ይሄን ሊንክ ጠቅ አድርገው ይከተሉና አዲሱ ገጻችንን ላይክ ያድረጉ! https://facebook/DimtsachinYisema2
Posted on: Thu, 01 Aug 2013 07:12:19 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015