የስኮትላንዳውያን መልዕክት ወደ ተለያዩ - TopicsExpress



          

የስኮትላንዳውያን መልዕክት ወደ ተለያዩ ተገንጣይ ቡድኖች በላይ ማናዬ የስኮትላንዳውያን ህዝበ ውሳኔ ህብረትን፣ አንድነትን በመወገን ተጠናቅቋል፡፡ ዩናይትድ ኪንግደምን ከተቀላቀለች 307 ዓመታትን ያስቆጠረችው ስኮትላንድ ‹ስኮትላንድ ነጻ ሀገር ትሁን ወይስ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ትቀጥል› በሚል ድምጽ እንዲሰጥ ተደርጎ አብላጫ ስኮትላንዳውያን በአንድነቱ ውስጥ መቀጠልን መርጠዋል፡፡ ውጤቱም ዛሬ ጠዋት ይፋ ተደርጓል፡፡ በ2011 ዓ.ም እ.ኤ.አ በስኮትላንድ የፓርላማ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማግኘት የቻለው የስኮትላንድ ናሽናል ፓርቲ በጊዜው ስኮትላንድ ነጻ ሀገር እንድትሆን ህዝበ ውሳኔ (Referendum) እንዲካሄድ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ፓርቲው በሚኒስትር አሌክስ ሳልሞንድ እየተመራ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሰረት ህዝበ ውሳኔው ትናንት ሀሙስ ተደርጎ ዛሬ አርብ መስከረም 9/2007 ዓ.ም ውጤቱ ይፋ ሆኗል፡፡ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው ጠቅላላ ህዝብ መካከል ከ85 በመቶ በላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡ የህዝበ ውሳኔው ቆጠራ እንደሚያመለክተውም ከ55 በመቶ በላይ ስኮትላንዳውያን ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር መቆየት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ቀድሞ ከተገመተው የ52 በመቶ የበለጠ መሆኑ ነው፡፡ ስኮትላንዳውያን ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ወይም ነጻ ሀገር መሆን እንፈልጋለን ወይስ በዚያው በህብረቱ መቀጠል ይሻለናል የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሱ የተደረጉበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ተጠቀሚነታችን የሚገባንን ያህል አይደለም ከሚል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ስምንት በመቶ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ስኮትላንዳውያን መካከል ሀገሪቱ ካላት ሀብት (resources) አንጻር ማግኘት ያለብን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መሻሻል አለበት የሚል ቅሬታ ያደረባቸው ወገኖች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከመካሄዱ በፊት በነበረው የየፊና የቅስቀሳ ስራ ወቅት ‹‹ስኮትላንድ የምትነጠል ከሆነ ራሴን እገድላለሁ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ለስኮትላናዳውያን የተለያዩ ማማለያዎችን ማቅረባቸውም ከዚሁ ስኮትላንዳውያን አለን ከሚሉት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ቅሬታ የመነጨ እንደሆነ ልብ ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝበ ውሳኔው በፊት ካሰሟቸው የማማለያ ንግግሮች በተቃራኒ ‹ማስፈራሪያ›ዎችም ነበሩበት፡፡ ‹‹ስኮትላንዳውያን ከህብረቱ መውጣትን ከመረጣችሁ እስከመጨረሻው ፍቺ እንደፈጸማችሁ ማወቅ ይኖርባችኋል›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዴቪድ ካሜሩን ስኮትላንድ ነጻ ሀገር መሆንን የምትመርጥ ከሆነ የህብረቱ መገበያያ የሆነውን ፓውን ስተርሊን መጠቀም እንደማይፈቀድላት አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ስኮትላንዳውያን ህብረትን፣ አንድነትን መርጠዋልና ማስፈራሪያው ተነስቷል፤ ማማለያው ግን ወደፊት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ስኮትላንዳውያን ሀገራቸው ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር እንደምትቀጥል መተማመኛ ድምጽ መስጠታቸውን ተከትሎ አንዳንዶች ‹ስኮትላንድም አልሄደች፣ ዴቪድ ካሜሩንም ራሳቸውን አይገድሉም› ሲሉ ቀልድ አዘል ትውስታ መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ስኮትላንድ ነጻ ሀገር ትሁን የሚለውን ሀሳብ ሲያቀነቅኑ የነበሩትና የቅስቀሳው ዋና መሪ የነበሩት ሚኒስትር አሌክስ ሳልሞንድ የህዝቡን ድምጽ አምነው ተቀብለው ከህብረቱ ጋር ተባብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ለህዝቡም የአንድነት ጥሪን አቅርበዋል፡፡ ዴቪድ ካሜሩንም ቢሆን በውጤቱ ደስተኛነታቸውን ገልጸው ‹ስኮትላንድ ነጻ ሀገር ትሁን› ለሚለው ድምጽ የሰጡትንም ‹‹ሰምተናችኋል›› ብለዋቸዋል በንግግራቸው፡፡ የስኮትላንዳውያን መልዕክት… ስኮትላንዳውያንን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩት የህብረቱ አባል ሀገራት ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌላው ዓለም ሁሉ ውጤቱን ሲጠብቀው እንደነበር ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይም የተገንጣይ አስተሳሰብን የሚያራምዱ አካላት ስኮትላንዳውያን የሚወስኑትን ውሳኔ እንደምርኩዝ ለመጠቀም ከማሰብ በሚመስል ሁኔታ በጉጉት ጠብቀውት ነበር፡፡ ከአውሮፓ ስፔንን መጥቀስ ይቻላል፤ የካታሎን ግዛት የመነጠል ጥያቄን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡ በእርግጥም ስኮትላንዳውያን የመነጠል ‹‹ነጻነት ጥያቄ›› ማንሳታቸው ጥያቄው በኋላ ቀር ሀገራት ብቻ የሚነሳ ጥያቄ አለመሆኑን እንደማስረጃ የሚያቀርቡ አልጠፉም፡፡ ዳሩ ግን ከመነጠል መጣመር አሽንፏል፡፡ ጥያቄውም ግልጽ ነበር፡፡ ‹‹ስኮትላንድ ነጻ ሀገር ትሁን ወይስ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ትቀጥል?›› የሚል ግልጽ ጥያቄ! ልክ የእኛና የኤርትራ ገዥዎች እንዳደረጉት ‹‹ባርነት ወይስ ነጻነት?›› የሚል ሆኖ አላየነውም፡፡ ከሂደቱ ግልጽነት አኳያም ስኮትላንዳውያን የምር የራሳቸውን ድምጽ በነጻነት የሰጡበት መሆኑን ልብ እንድንል እድል የሰጠ መሆኑን ማየት ችለናል፡፡ የስኮትላንድ ህዝበ ውሳኔ በግልጽ የነገረን መልዕክት ዴሞክራሲና ነጻነት ባለበት ሀገር ህዝብ መነጠልን ሳይሆን አንድነትን እንደሚፈልግ ነው፡፡ የመነጠል ጣጣ የሚመጣው ከጭቆና፣ ህዝብን በከንቱ ግብታዊነት እናውቅልሃለን ከማለት መሆኑን ልብ እንድንል የረዳን ይመስለኛል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብቻ 31 ሀገራት ተገንጥለው ራሳቸውን የቻሉ ሀገራት ሆነዋል፡፡ የሁሉም የመገንጠል መነሻ ግን ጭቆና ነበር፤ ነውም፡፡ የሶብየት ህብረት መፈራረስ፣ የዩጎዝላቪያ መነጣጠል መነሻቸው የርዕዮተ ዓለም መውደቅ እንዳለ ሆኖ በውስጣቸው ሰፍኖ የነበረው የበዛ ጭቆና መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ የቅርብ ጊዜውን የደቡብ ሱዳንን እንኳ ብናይ መነጠልን ምርጫቸው ያደረጉት ከጭቆና ብዛት የተነሳ ነው፡፡ በዚህም የተሻለን ነጻነት በማለም ህዝቡ መገንጠልን ምርጫው አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ መነጠል በራሱ ግብ ባይሆንም! ይህን ደግሞ በዚህቺው በደቡብ ሱዳን እና በኤርትራ እያየን ያለነው ሀቅ ሆኗል፡፡ ስኮትላንዳውያን ቀድሞውንም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ናቸውና ህብረትን መርጠዋል፡፡ አጣነው የሚሉት ነጻነት አልነበረምና ህብረትን መርጠዋል፡፡ ጥያቄው ግን በጥቂት ቡድኖች ተነስቶ እነዚህ ቡድኖች በሰሩት የቅስቀሳ ስራ ወደ ህዝበ ውሳኔ ሊያመራ ችሏል፡፡ ይህ ግን ብዙሃኑን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ህዝብ አንድነቱን በነጻነት ማጣጣሙን ሊዘነጋው አልቻለምና! ኬንያ ውስጥ የሚኖሩ የኬንያ ሶማሌዎች ቀደም ባለው ጊዜ (ኬንያ በጎሳ ግጭት በገባችበት ወቅት) የመነጠል ጥያቄ ያነሱ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ጥያቄውም የብዙዎች ነበር፡፡ አሁን ኬንያ የተሻለ ዴሞክራሲንና ነጻነትን ማስፈን በመቻሏ እነዚህ የኬንያ ሶማሌዎች በኬንያ ውስጥ መኖርን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ የመነጠል ጥያቄው ከስሟል ማለት ባይቻልም ብዙሃኑ ግን ነጻነትን ባገኘበት ኬንያ መቆየትን እንደሚፈልግ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም አንዳንድ ቡድኖች የመነጠልን አጀንዳ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ በይፋ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በእርግጥ የእነዚህ ወገኖች አካሄድ ኃይልን ምርጫው ያደረገ በመሆኑ የተለየ ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወገኖች የሚያነሱትን ጥያቄ የመመለሻው ቁልፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲና የተሻለ ነጻነትን ማስፈን እንደሆነ ስኮትላንዳውያን ሂደቱ ውስጥ ከገቡም በኋላ የሰጡትን ድምጽ አይቶ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፡፡ ስለሆነም የእያንዳንዱ የመነጠል ጥያቄ መነሻም ሆነ መድረሻ ጭቆና መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡ እናም ህዝብ የሚሻውን ነጻነት፣ ዴምክራሲ ከተጎናጸፈ ምንግዜም ህብረትን፣ አብሮ መኖርን፣ አንድነትን ምርጫው ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ ለመነጠል መነሻ የሆነውን ጭቆና የማስወገዱ ስራም በተናጠል ሳይሆን በጋራ መሰራት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
Posted on: Fri, 19 Sep 2014 08:30:23 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015