ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ - TopicsExpress



          

ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ዘውዴ ይመኑ እና ከእናቱ ወ/ሮ አማረች ተፈራ የምሩ ጥቅምት 12 ቀን 1967 ዓ.ም በጭናቅሰን ገብርኤል ጅጅጋ ከተማ ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጅጅጋ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከፊል የሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን ደግሞ ከወላጅ አባቱ ጋር ወደ አስመራ በመሄድ የተከታተለ ሲሆን፤ ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ጅጅጋ በመመለስ ተምሯል፡፡ በ1991 ዓ.ም. በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡ ፈቃደኛ ሰዎች በማግኘቱ እራሱን ያስተዳድርበት የነበረውን የፎቶግራፍ አንሺነት ሥራን ትቶ በሃያ አራት (24) ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የያኔው ፋልከን ክለብ ድምጻዊነቱን “ሀ” ብሎ ጀመረ፡፡ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ አልበሙን እስካወጣበት 2000 ዓ.ም ድረስ የሌሎች ድምጻውያንን ሥራዎች ፣ በዋነኝነት የአሊ ቢራን እና የቦብ ማርሊን ዘፈኖችን ይዘፍን የነበረ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ዱባይም በመመላለስ በድምጻዊነቱ ሰርቷል፡፡ በጥቅምት 2000 ዓ.ም በአብዛኛው በሬጌ ስልት የተዘጋጀውን “እንደ ቃል” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙ ከተለቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ መጠን በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ ጣዕም የመጣው “እንደ ቃል” አልበም በኢትዮያ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ ይበልጥ ይወደድ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ከዚህ አልበሙ በኋላ በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሙዚቃ ዝገጅቶችን እያቀረበ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የሙዚቃ ቦታዎች ላይም ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት የራሱን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ በመድረክ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ አልበሙንም በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን በድንገት እስኪታመም ድረስ ሙሉ ትኩረቱ በዚሁ ሥራው ላይ ነበር፡፡ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በድንገተኛ የስትሮክ ህመም መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ የወደቀ ሲሆን ፤ ህመሙ ጠንቶ እራሱን ሳያውቅ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረገልት ቆይቶ በወዳጅ ዘመዶቹ ርብርብ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ናይሮቢ ኬንያ በአጋ ካን ሆስፒታል በማቅናት ሕይወቱን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በታመመ በአምሰተኛ (5ኛ) ቀኑ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት በ38 ዓመቱ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነበር። የድምጻዊ እዮብ መኮንን የቀብር ስነ-ስርዓት በዛሬው እለት በነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂቆቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ለእዮብ መኮንን ቤተሰብ ፤ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን፡፡ Must share to ur friend !!!
Posted on: Wed, 21 Aug 2013 20:13:36 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015