ድምፃችን ይሰማ #EthioMuslims #Review ዳሰሳ - - TopicsExpress



          

ድምፃችን ይሰማ #EthioMuslims #Review ዳሰሳ - አዲስ ፕሮግራም! እሁድ ነሃሴ 25/2006 በድምፃችን ይሰማ የፌስ ቡክ ገፅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቋሚነት የሚስተናገዱ ፕሮግራሞች መኖራቸው ይታወሳል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በየሳምንቱ ጁመዓ የሚቀርበው ነሲሃ፣ በየሳምንቱ ሰኞ የሚዘጋጀው የህገ መንግስት ስልጠና ለ‹‹ህግ አስከባሪዎች›› እና በየሳምንቱ እሁድ የሚቀርበው የሳምንቱን ዋና ዋና ዜናዎች በከፊል የምናይበት ፕሮግራም ይገኙበታል፡፡ ዛሬ ደግሞ በአላህ ፈቃድ ሌላ አዲስ ተከታታይ ፕሮግራም ጀምረናል፡፡ ፕሮግራሙ ‹‹ዳሰሳ›› በሚል የተሰየመ ሲሆን በተመረጡ ወቅቶች እየተዘጋጀ የሚቀርብ በአዲስ አበባ እና በክልሎች መሳጂዶቻችንን፣ አካባቢያችንን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ህይወታችንን በተጨባጭ እየቃኘ ትንተና የሚያቀርብ ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ ሰላማዊ ትግላችን ዘላቂ መብቶችን ለማስከበር በሚያደርገው ሽግግር ውስጥ በህብረተሰባችን ውስጥ የሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎችን እየዳሰሱ እና ግንዛቤ እያሰፉ ሁላችንም በተግባር በምናውቀው እውነታ ላይ ተመስርተን ቀጣይ ተግላችንን ይበለጥ የተናበበ ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ የዛሬው የዳሰሳ ፕሮግራማች ባሳለፍነው ጁመዓ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኙ መሳጂዶች የቀረቡ ኹጥባዎችን አንኳር መልዕክት እና ጭብጥ በወፍ በረር ይቃኛል፡፡ ***************************************** ዳሰሳ (ክፍል 1) ጁምዐ የሙስሊሞች ዒድ ነው - የጋራ ትጋታችንን እንድናሳይ በአላህ የታዘዝንበት እና የሰራናቸውን ስራዎች የምናወራርድበት ዕለት! በተጨማሪም ጁሙዐ መንፈሳዊ ወንድማማችነትና ማህበራዊ አብሮነት የሚንፀባረቅበት እና ለአላህ ትዕዛዝ አዳሪ መሆናችን በተግባር የሚገለፅበት ልዩ ቀን ነው፡፡ የጁመዐ አብይ አካል የሆነው ደግሞ ኹጥባ ነው፡፡ ኹጥባ ሰሞንኛ ጉዳዮች በቁርአንና ሀዲስ መነፅር የሚቃኙበትና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሳምንት የሚሆነውን መንፈሳዊ ስንቅ የሚያስቋጥር ምክር ነው፡፡ በዚህ የዳሰሳ መሰናዶ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኙ መሳጂዶች በዚህ ሳምንት የነበሩ ኹጥባዎችን አንኳር መልዕክት እና ጭብጥ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡ (ክፍለ ከተማው ውስጥ 19 መስጂዶች ሲኖሩ ጁሙዓ የሚሰገደው በአስራ አንዱ ነው፡፡) *** የመጀመሪያ ዳሰሳችን መሳለሚያ ወደሚገኘው ካሊድ ኢብኑል ወሊድ (01) መስጂድ ያቀናል፡፡ በመጀመሪያ የኹጥባው ክፍል ኢማሙ ሙስሊሙ በየትኛውም ቦታና ጊዜ አላህን መፍራት እንዳለበት ያስታወሱ ሲሆን ያለንበትን ዙልቂዕዳ ወር ትልቅነት በማውሳት ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ወር ዑምራ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ በሁለተኛው የኹጥባው ክፍል የተፈጠርንለትን አላህን የማምለክ አላማና ምድር ላይ የእርሱ አምባሳደር የመሆን ተልዕኮን በአግባቡ በመወጣት ከአላህ ጋርም ሆነ ከሰዎች ጋር በሚኖረን መስተጋብር አላህን መፍራት እንደሚገባ፣ ብሎም የሰው ልጅ ይህች አለም ከእነዚህ ታላላቅ አላማዎቹ እንዳትጎትተው በመጠንቀቅ ለመጪው ህይወት መሸጋገሪያ ድልድይ እንዲያደርጋት በማስታወስ የጁመአ ኹጥባቸውን አጠናቀዋል፡፡ *** እዚያው መሳለሚያ የሚገኘው መስጂድ ቢላል ኹጥባ ርዕስ ደግሞ ዱዐ የነበረ ሲሆን የዱዐ ትሩፋቶች እና ዱዐ ተቀባይነት የሚያገኝባቸው ወቅቶች ተብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም መልካም ስራቸው ከማይቋረጥባቸው ሰዎች መካከል መልካም ልጁ ዱዐ የሚያደርግለት ሰው ስለመሆኑ የሚገልጸውን ነብያዊ ሀዲስ በመጥቀስ የዱዐን ደረጃ አመላክተዋል፡፡ *** ኳስ ሜዳ የሚገኘው ሀጂ ዘይኑ መስጂድ የመጀመሪያው ኹጥባ ጭብጥ በአላህ መንገድ ላይ የመታገል እና የዚህ ዑማ ምርጥነት መገለጫ በሆነው በመልካም የማዘዝና ከመጥፎ የመከልከል አስፈላጊነትን የተመለከተ ነበር፡፡ በአምልኮ ላይ መጠንከር እንደሚገባ ኢማሙ አደራ ብለዋል፡፡ በሁለተኛው የኹጥባ ክፍል ከእምነት መሰረቶች አንዱ እና አቅም ባለው ሰው ላይ በህይወት አንድ ጊዜ ማድረግ የነፍስ ወከፍ ግዴታ ሰለሆነው ሀጅ አፈፃፀምና ሀጅ ማድረግም የሚያስገነው ትሩፋት ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ኢማሙ የተሰተካከለ ሀጅ ማድረግ ወንጀልን በሙሉ እንደሚያስምር ነብያዊውን ሀዲስ አውስተው ሰዎች ወደ ሀጅ እንዲሄዱ፣ እንዲሁም ኒያቸውን እንዲያስተካክሉ አስታውሰው ኹጥባው ተጠናቋል፡፡ *** በሌላ በኩል ከሀጂ ዘይኑ መስጂድ በተወሰነ ርቀት ላይ የሚገኘው የሀጂ ዩኑስ የጁሙዐ ኹጥባ በሁለቱም ክፍሎች ስለ ሀጅና ስነ-ስርዐቱ ያወሳ ነበር፡፡ ኹጥባ አድራጊው የሀጅን ትሩፋት እና ደረጃ፣ እንዲሁም የአላህ መልዕከተኛ ‹‹ሀጅጃችሁን ከእኔ ያዙ›› ባሉት ንግግር ላይ መሰረት በማድረግ የሀጅን ስነ-ስርዐት አብሯርተዋል፡፡ ‹‹ኢህራም ለብሼ የአላህን ቤት ስረግጥ የሚሰማኝን ደስታ አጣጥሜ ብሞትም አያስጨንቀኝም›› በማለት ሰው ለሀጅ እንዲነሳሳ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ *** የመርካቶ ባዩሽ ኹጥባ እጅግ መሳጭ እና ረዘም ያለ የነበረ ሲሆን አብይ ርዕሱ ‹‹ዙልም›› (በደል) ነበር፡፡ ኹጥባ አድራጊው ዙልም በሶስት እንደሚከፈል አውስቶ እያንዳንዱን በደል በዝርዝር አብራርቷል፡፡ የመጀመሪያውና ከባዱ በደል አላህን መበደል ሲሆን ይህም ህልውናህን ያስገኘ፣ ተንከባካቢና መጋቢ፣ ህይወት ሰጪና ነሺ አላህ ሆኖ ሳለ በርሱ ላይ ማጋራት ነው፡፡ የዚህ በደል ባለቤት የአላህን ምህረት የማያገኝና በቅጣትም ውስጥ ዘውታሪ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ሁለተኛው በደል ራስን መበደል ሲሆን ይህም አላህ ዕርም ያደረጋቸውን ነገሮች በመዳፈር፣ ከትዕዛዛቱ በማፈንገጥ ወንጀል መስራት ነው፡፡ ይህን የበደል አይነት አላህ ባርያውን ከፈለገ ይምረዋል፤ ከፈለገም ይቀጣዋል፡፡ ሶስተኛውና ኢማሙ በአንክሮ ያብራሩት የበደል አይነት ሌሎችን መበደል ነው፡፡ ይህ በደል በተለይ በንግድ ቦታዎች የሚስተዋል ሲሆን የተበላሸና ጊዜው ያለፈበት ዕቃ መሸጥን፣ የስሪት ሀገሩን በመቀየር ማጭበርበርን እንደምሳሌ በመጥቀስ የበደሉን መበራከትና አደገኛነት ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪ በእጅና በምላስ፣ አልያም በማንኛውም መልኩ በሌሎች ላይ የሚደርስ በደል የከፋ መሆኑን ገልፀው በተለይ ሀሜትን አውግዘዋል፡፡ *** የሸኽ አወል መስጂድ ኹጥባ በሰብር ዙሪያ የነበረ ሲሆን የሰብር ደረጃና ትሩፋት ተብራርቷል፡፡ አሁን ያለንበት ወር ከአራቱ የተከበሩ ወራቶች አንዱ የሆነው ዙልቀዒዳ እንደመሆኑ መጠን ወደ አላህ ሙሉ ለሙሉ መመለስና ለወንጀሎቻችን ምህረትን መጠየቅ ተገቢ መሆኑ ተወስቷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ በተከበረ ወር መልካም ስራ ማብዛት ተገቢ እንደሆነ በመጥቀስ ለወላጅ በጎ መዋል፣ የተቸገረን መርዳት፣ በሱና አምልኮዎች ላይ መበርታትን የመሰሉ መልካም ስራዎችን ትኩረት ሰጥተን ልንፈፅማቸው እንደሚገባ ኢማሙ አስታውሰዋል፡፡ ሀሰት መናገር፣ ቅጥ ያጣ አለባበስ፣ ሀራም መመገብ እና የመሳሰሉትን የተወገዙ ተግባራት በመጥቀስም ህዝቡ ሊርቃቸው እንደሚገባ መክረዋል፡፡ *** የአንዋር መስጂዱ ኹጥባ ለአሚር መታዘዝና ያለንበት ወር ልቅና ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ በተለይ ያለንበት ወር ከምንጊዜውም በላይ ወደ አላህ ለመቃረብ ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ በመልካም ስራ ላይ መበርታትና ከዕኩይ ተግባራት በመታቀብ፣ እንዲሁም ለሌሎች መልካም በመዋል ማሳለፍ ተገቢ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ለዚክር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተያይዞ ተጠቅሷል፡፡ *** የረያን መስጂድ ኹጥባ በመጀመሪያ ክፍሉ ሰዎች ባጠቃላይ አላህን ተገቢውን ያህል ልንፈራው እንደሚገባ እና ያለንበትን ወር ልቅና አስመልክቶ ገለጻ የተደረገበት ሲሆን እያንዳንዱ ሙስሊምም በዚህ ወር በመልካም ስራዎች ላይ እንዲበራታ፣ ከእኩይ ስራዎችም እንዲርቅ አደራ ተብሏል፡፡ ዱዐ፣ ዚክር፣ የቲሞችን መርዳትና መንከባከብ፣ የታመሙን መጠየቅ ትከረት ሊሰጣቸው የሚገቡ መልካም ስራዎች መሆናቸውም ተወስቷል፡፡ በሁለተኛው የኹጥባ ክፍል ከዚህ ወር መገባደድ በኋላ ስለሚመጣው ሀጅ የነበረ ሲሆን ስለትሩፋቶቹና ስነ-ስርአቱ በማውሳትም ኹጥባው ተጠቃሏል፡፡ *** *** ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል! ድምፃችን ይሰማ! አላሁ አክበር!
Posted on: Sun, 31 Aug 2014 13:42:36 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015