ጀብሃ እና ሻዕቢያ (1961-1991 G.C) ጸሓፊ፡ - TopicsExpress



          

ጀብሃ እና ሻዕቢያ (1961-1991 G.C) ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ------ ክፍል አምስት ----- በትናንትናው ጽሑፌ ስለ“መንካዕ” ንቅናቄ ታሪክ አውግቼአችሁ ነበር፡፡ የዛሬው ጽሑፍ ደግሞ ከመንካዕ በኋላ በሻዕቢያ ውስጥ በታዩ ሁለት መለስተኛ ንቅናቄዎች ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህ ንቅናቄዎች የመንካዕን ያህል ጥንካሬ አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ከሻዕቢያ ጋር ሁሌ የሚጠቀሱ በመሆናቸው ልንዳስሳቸው ግድ ይለናል፡፡ === የ“ብጽኣይ” እንቅስቃሴ==== በሻዕቢያ ውስጥ የፈነዳው የመንካዕ ንቅናቄ ከተዳፈነ በኋላ የድርጅቱ ታጋዮች ማጉረምረማቸውን አላቆሙም፡፡ በተለይ የመንካዕ መሪዎችን የገጠማቸው ሰቆቃ የተመላበት እስርና የሞት ቅጣት ብዙዎቹን አስከፍቷል፡፡ ሆኖም ታጋዩ እርስ በራሱ ይጠራጠር ስለነበር ድምጹን ከፍ አድርጎ አላሰማም፡፡ በዕድሜው ጠና ያለ አንድ ታጋይ ግን “ድርጅቱ ውስጣዊ ዲሞክራሲ እንዲኖረው አደርጋለሁ” በማለት የበኩሉን ጥረት ለማድረግ ተነሳ፡፡ ያ ታጋይ ጎይቶም በርሄ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሩቅ ነው፡፡ ሻዕቢያን የተቀላቀለው በ1972 ነው፡፡ ይህ ሰው ከፍተኛ የሆነ የስነ-ጽሑፍና የርዕዮተ ዓለም ትንታኔ ችሎታ ነበረው፡፡ በዘመኑ እጅግ በጣም ይፈለጉ የነበሩትን ማርክሳዊና የዲያሌክቲክ ፍልስፍና መጻሕፍትን ከውጪ ቋንቋዎች ወደ ትግርኛ ተርጉሟል፡፡ እርሱ ራሱ ከጻፋቸው ኦሪጂናል ጽሑፎች መካከል ደግሞ “መን እዩ ብፅአዊ? መን እዩ ሰውራዊ?” (“ጓድ” ማለት ማን ነው? አብዮታዊውስ ማን ነው?) የሚል ርዕስ ያለው ባለ 30 ገጽ መጣጥፍ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረው የታሪክ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ሻዕቢያ የርሱን ጽሑፎች ታጋዩን ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ይህ ሰው በዕድሜውም ሆነ በተሰጥኦው አንቱታን ያገኘ ስለሆነ ሁሉም ታጋዮች “ብጽአይ” (ጓድ) በማለት ነበር የሚጠሩት፡፡ “ብጽአይ” ጎይቶም በመንካዕ ንቅናቄ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላደረገም፡፡ ሆኖም ውጥረቱን እንዲሸመግሉ ከተመረጡ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እነ ኢሳያስ የመንካዕ መሪዎችን በከባድ ቅጣት ዝም ሲያሰኟቸው ግን “የተሰጠው ፍርድ ኢ-ፍትሓዊ ነው” በሚል ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ በዚህም ከሃላፊነት እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ ታዲያ ብፅአይ ጎይቶም ስልጣኔን ተቀማሁ ብሎ ወደ ኩርፊያ አልሄደም፡፡ ድምጹን አጥፍቶ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ የሚሰፍነበትን መንገድ ያውጠነጥን ነበር፡፡ በ1975 መጨረሻ ላይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩ ጥቂት ጓዶች ግንባሩን ሲቀላቀሉ ከነርሱ ጋር መቀራረብ ጀመረ፡፡ ከተማሪዎቹ ጋር ባደረገው ውይይትም “ድርጅቱን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለብን” የሚል አጀንዳ አስታጠቃቸው፡፡ እነዚያ ወጣቶችም የርሱን ሀሳብ ማቀንቀን ጀመሩ፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ታጋዩን ማወያየትና ድጋፍ ማሰባሰብ ሞከሩ፡፡ አንዳንዶች ወደነርሱ ተጠጉ፡፡ ብዙዎቹ ግን የመንካዕ ትውስታ ከአዕምሮአቸው ያልጠፋ በመሆኑ ወደ ብጽአይ ጎይቶምና ጓዶቹ ለመጠጋት አልፈቀዱም፡፡ እነ ብጽአይ ግን ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ በርካታ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድጋፍ ሰጡአቸው፡፡ ሆኖም ዓላማቸውን በሚያስፈጽሙበት መንገድ ላይ በመምከር ላይ ሳለ ግን በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የስለላ መረቡን በሁሉም የሻዕቢያ ታጋዮች ላይ እንደ ሸረሪት ድር ያደራው የ“ሀላዋ ሰውራ” አዳኞች በቀላሉ “ቀጨም” አደረጓቸው፡፡ የንቅናቄው መሪዎችና ተባባሪዎች የተባሉት በሙሉ እየተፈለጉ ታሰሩ፡፡ የ“ሀለዋ ሰውራ” ኃላፊዎች ብጽአይ ጎይቶምንና ጓዶቹን ለአራት ዓመታት በእስር ካቆዩአቸው በኋላ በ1980 በሞት ቀጡአቸው፡፡ ብጽአይ ጎይቶም የተረጎማቸው መጻሕፍትና በራሪ ወረቀቶችም ከያሉበት እየተሰበሰቡ ተቃጠሉ፡፡ በጎይቶም ጽሑፎች የተበላሸውን የታጋይ አዕምሮ ለማደስ በሚልም ስታሊናዊ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ድርሰቶች በብዛት እንዲተረጎሙ ተደረጉ (የትርጉም ስራውን በዋናነት ያከናወነው በ1985 ገደማ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር የነበረውና አሁን በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ሀይሌ መንቆርዮስ እንደሆነ ይነገራል)፡፡ ***** ይህ ብዙ ሳይራመድ በእንጭጩ የተቀጨው ንቅናቄ “ብፅአይ ምንቕስቓስ” ይባላል፡፡ “የጓዱ እንቅስቃሴ” ማለት ነው፡፡ “ጓድ” ወይንም “ብፅአይ” ተብሎ የሚጠራው ጎይቶም በርሄ ነው፡፡ ከርሱ ጋር በቅርበት ሆኖ እንቅስቃሴውን መርቷል የሚባለው ደግሞ ዓለም አብርሃ የተባለ ታጋይ ነው፡፡ እነዚህ ጓዶች እንደ “መንካዕ” ንቅናቄ መሪዎች “የድርጅቱ አመራር ከስልጣን ይውረድልን” አላሉም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ለመጠየቅ ብቻ ነበር የተነሱት፡፡ ሆኖም የሰልፊ ነጻነት መሪዎች በእንቅስቃሴው አልተደሰቱም፡፡ እንዲያውም የድርጅቱን ህልውና የሚያናጋ መናፍቃዊ ንቅናቄ አድርገው ነው የወሰዱት፡፡ ሻዕቢያዎች “የብፅአይ ምንቕስቃስ” መሪዎች “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ (ERP) የተባለ ህገ-ወጥ ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ አቋቁመዋል፤ የታወቀውን የግንባሩን ሶቪየት ቀመስ የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ በመቀልበስ የሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግን መስመር ለማስፈን ሞክረዋል፤ በመሆኑም የሞት ቅጣት መፈጸሙ በግንባሩ ህግ መሰረት ተገቢ ነው” ይላሉ፡፡ ሆኖም ይህ “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ” የተሰኘ ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ ስለመፈጠሩ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በዚህ ንቅናቄ ጦስ ታስረው ህይወታቸው ካለፈው ታጋዮች መካከል ጎይቶም በርሄ (“ብፅአይ”)፣ ዓለም አብረሃ፣ መሲህ ርዕሶም፣ ተክላይ ገብረ ክርስቶስ፣ ሚካኤል በረከተአብ፣ ሀይሌ ዮሐንሶም፣ ሳሙኤል ገብረ ድንግል፣ በረከት ሀይሌ፣ ሀይሌ ሀብተጽዮን እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ ተወልደ እዮብ የሚባለው የቀድሞው የድርጅቱ ቁልፍ ሰውም ከነዚህ ሴረኞች ጋር አብረሃል በሚል በጥይት ተደብድቦ ተረሽኗል (እነዚህ ታጋዮች የተረሸኑት በ1980 ሳሕል በረሃ ውስጥ በሚገኘው አራግ በተሰኘ ቀበሌ ነው)፡፡ === የ“የማናዊ” (ቀኝ መንገደኞች) እንቅስቃሴ==== ይህኛው እንቅስቃሴ የብጽዓይ ንቅናቄ ተከታይ ሆኖ ነው የፈነዳው፡፡ ንቅናቄው የተካሄደው “ሰልፊ ነጻነት” እና “ህዝባዊ” ሀይሊ በይፋ ተዋህደው “ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ” የተሰኘውን ግንባር መፍጠራቸው ከተነገረበት ጊዜ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው (በተጨማሪም በዚያ በወቅት (1977-78) ብዙዎቹ የኤርትራ ከተሞች ከመንግሥት እጅ በመውጣት በሻዕቢያ እና ጀብሃ ቁጥጥር ስር ገብተው ነበር)፡፡ በዚህ ንቅናቄ ገፍቶ የወጣው ዋነኛ ጥያቄ “በግንባሩ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ሙስናና ብልሹ አሰራር ይወገድ” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ንቅናቄ ጀማሪ ማን እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ በንቅናቄው ውስጥ ከተሳተፉት ግንባር ቀደም መሪዎች መካከል ዶ/ር እዮብ ገብረ-ልዑል፣ መሓሪ ግርማ-ጽዮን፣ ገብረ-ሚካኤል መሐሪ-እዝጊ፣ ህብረት ተስፋ-ጋብር፣ ኪዳኔ አቤቶ፣ ፍሥሐዬ ኪዳኔ፣ አርአያ ሰመረ፣ አማኑኤል ፊላንሳ የተባሉት ይጠቀሳሉ (ብዙዎቹ በአውሮጳ ሀገራት የተማሩ ናቸው)፡፡ የሻዕቢያ መሪዎች በንቅናቄው የተሳተፉ ታጋዮችን “የቀይ መንገደኛነት ፈለግ ተከታዮች” በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ እነዚያ የንቅናቄ መሪዎች ጥያቄዎቻቸውን ለሻዕቢያ አመራር ባቀረቡ ማግስት ነው የታሰሩት፡፡ ታዲያ ንቅናቄው ከተዳፈነና ሻዕቢያ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ የቀድሞ የግንባሩ ቀንደኛ መሪ እና የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ የነበረው ሰለሞን ወልደማሪያምም ከንቅናቄው ጋር ንክኪ አለው ተብሎ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የግንባሩ ዋነኛ መርማሪ የነበረው ሀይሌ ጀብሃም በዚያው ወቅት እንዲታሰር ተደርጓል፡፡ ሀይሌ ጀብሃ የታሰረው “በእስረኞች ላይ ከመጠኑ ያለፈ ኢ-ሰብአዊ ሰቆቃ ይፈጽማል” በሚል ምክንያት ነው፡፡ በርግጥም በርካታ ኤርትራዊያን ስለርሱ ጭካኔና ገዳይነት በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ እውቁ ኤርትራዊ ምሁር ዶ/ር በረከት ሀብተስላሴ በቅርቡ ከአንድ ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀይሌ ጀብሃ አንዱን እስረኛ በብትር ጭንቅላቱን እየቀጠቀጠ ሲመረምረው ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ ሰለሞን ወልደማሪያም የታሰረበት ምክንያት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰለሞን ወልደማሪያም በግንባሩ ውስጥ የነበረው ተፈላጊነት እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች የታዩት ቀደም ብለው ነው፡፡ ለምሳሌ በ1975 መጨረሻ ላይ ለህክምና ፖርት ሱዳን ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ቁልፍ ከሆኑ የድርጅቱ የስልጣን ቦታዎች ተገፍቶ የካድሬ ትምህርት ቤት አሰልጣኝ እንዲሆን ተመድቧል፡፡ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊነቱንም ከህዝባዊ ሀይሊ ለመጣው ዓሊ ሰዒድ አብደላ አስረክቧል፡፡ እርሱ ግን የድርጅቱ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ የግንባሩ መሪዎች ይከዱኛል የሚል ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ ለሰለሞን ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ የታየው 37 አባላት ያሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ በዚያ ምርጫ ላይ ሰለሞን በእጩነት ሲጠቆም ካድሬው በከፍተኛ ጩኸት ተቃውሞውን እንደገለጸ ይወሳል፡፡ አንዳንድ ካድሬዎች ከመቀመጫቸው እየተነሱ “ይህ ሰው የቀኝ መንገደኞቹ አንጃ መሪ ነው፤ ለርሱ እስር ቤት እንጂ ስልጣን አይገባውም” የሚል ሐሳብ መስጠታቸው ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከኢሳያስ አፈወርቂ በፊት ወደ ዓላ በረሃ ሄዶ ከጥቂት ወጣቶች ጋር “ሰልፊ ነጻነት” የተባለውን ቡድን የመሰረተው ሰለሞን ወልደማሪያም “አዛዥ ናዛዥ” ሆኖ ብዙዎችን ካንቀጠቀጠበት መንበረ ስልጣን ላይ ተገፍትሮ ወደታች ተወርውሯል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ሰለሞንን ከስልጣኑ ያስነሳው “ይህ ወጣት በድርጅቱ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን በመዳፉ ጠቅልሎ በመያዙ ወደፊት ከሊቀመንበርነቴ ያባረኛል” የሚል ስጋት ስለገባው መሆኑን ታሪኩን የሚያውቁ ምስክሮች ያስረዳሉ፡፡ በርግጥም ሰለሞን በሰልፊ ነጻነት ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ሰው ነበር፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ የቡድኑ መሪ ሆኖ ቢቀመጥም ድርጅቱን በቀጥታ የሚመራው ሰለሞን ወልደማሪያም ነበር፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ አባል የነበሩት አቶ አድሓኖም ፍትዊ የተባሉ ኤርትራዊ በጊዜው የነበረውን የስልጣን ክፍፍል ሲያስረዱ “ሰለሞን ሁሉንም ነገር ነበር፤ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሐፊ ነው፡፡ ወታደራዊ አዛዥም ነው፤ የስልጠና ማዕከል ሀላፊም ነው፤ የጠቅላይ እዙ የበላይ አዛዥም ነበር፤ በግንባር ያለውን ጦር የሚያንቀሳቅሰው እርሱ ነው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ለስም ብቻ ነው ሊቀመንበር ሆኖ የተቀመጠው” በማለት አስረድተዋል፡፡ ታዲያ ኢሳያስ ሰለሞንን ከስልጣን ያስነሳው ብልጠት በተመላበት ዘዴ ነው፡፡ ሰለሞን ለረጅም ጊዜ የጉበት በሽተኛ እንደሆነ ስለሚታወቅ “እስከዛሬ ድረስ ለኛ ስትል ደክመሃል፤ አሁን ግን መታከም አለብህ፤ ህክምና እያለ መሞት የለብህም፤ ሱዳን ሄደህ ከፍተኛ ሐኪም መጎብኘት አለብህ” አለው፡፡ በተጨማሪም “ኡሥማን ሳልህ ሳቤ የድርጅታችንን የእርዳታ መስመር ስለዘጋብን ወደ ውጪ ሄደህ እርሱንም ማስከፈት አለብህ፤ ይህንን ማድረግ የምትችለው አንተ ብቻ ነህ” በማለት አከለበት፡፡ ሰለሞን የኢሳያስን ምክር ሲሰማ በልቡ ኩራት ተሰማው፡፡ “ለካስ እንዲህ ዓይነት ትልቅና ተፈላጊ ሰው ኑሬአለሁ?” በማለት ተንጠራራ፡፡ ወዲያኑ ስልጣኑን በሙሉ ለኢሳያስና ለተከታዮቹ አስረክቦ ወደ ፖርት ሱዳን ሄደ፡፡ እነ ኢሳያስም የርሱን እግር ተከትለው በድርጅቱ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ሰዎቻቸውን አስቀመጡ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የሰለሞንን ግለኝነትና የስልጣን ጥመኛነት የሚያስረዳ ፕሮፓጋንዳ በሰፊው ተናፈሰ፡፡ ታዲያ ታጋዩም ሰለሞንን በፊቱኑ ይጠላው ነበርና ፕሮፓጋንዳውን ሲሰማ “ይህ አምባገነን! እርሱ ነው ለካስ ሁሉንም ሲቆላልፍ የነበረው” በማለት ተራገመ፡፡ ሰለሞን ህክምናውን ጨርሶ ከሱዳን መጣ፡፡ እነ ኢሳያስ ስልጣኔን ያስረክቡኛል ብሎ ሲጠብቅ “ላንተ እረፍት ስለሚያስፈልግህ የድርጅቱ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ ቀለል ባለው የካድሬ ስልጠና ስራ ላይ መድበንሃል” አሉት፡፡ ሰለሞንም ምንም ሳይጠራጠር በስልጠና ስራ ላይ ተሰማራ፡፡ የድርጅቱ ጉባኤ ተካሂዶ በድርጅታዊ መንገድ በተካሄደው ምርጫ ከአመራሩ ሲወገድ ግን ከእንቅልፉ ባነነ፡፡ “የገዛ ወዳጆቼ ተጫወቱብኝ እያለ” ተቆጨ፡፡ ከዚያ በኋላ ነገረ-ስራው ሁሉ የግንባሩን መሪዎች በአደባባይ መሄስና ማብጠልጠል ሆነ፡፡ እርሱ ራሱ ያጠፋቸውንም ጥፋቶች በግልጽ ማውገዝ ጀመረ፡፡ በተለይ በከረን ከተማ በተደረገ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ስለ መንካዕ ንቅናቄ መሪዎች ሲጠየቅ “የተሰጠው ፍርድ ትክክል አይደለም፤ የህዝብ ልጆችን ገድለን ቀብረናል” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ ታዲያ እርሱ በየወረዳው እየሄደ የሚናገረው ንግግር ወደነ ኢሳያስ ይደርስ ሰለነበር መላ እንዲበጅለት ተወሰነ፡፡ ካድሬዎች በድርጅቱ ጉባኤ ላይ ያነሱትን ክስ እንደ አዲስ በማንቀሳቀስ “የየማናዊ ምንቓስቓስ ደጋፊ ነህ” ተብሎ ታሰረ፡፡ ለአራት ዓመታት በሀለዋ ሰውራ ከቆየ በኋላ በ1983 ሳህል ውስጥ ሀክሺብ በተባለ ስፍራ ተረሸነ፡፡ ***** በሰለሞን ወልደማሪያም ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ አይበዛበትም፡፡ ይህ ፍርድ እርሱ ራሱ በ“ሀለዋ ሰውራ” ሲፈጽመው ከነበረው ምህረት የለሽ ሰቆቃ እና ርሸና ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ችግሩ ግን ፍርዱ በስነ-አመክኖአዊ መንገድ ያልመጣ መሆኑ ነው፡፡ የሻዕቢያ ሰዎች ሰለሞንን የረሸኑት በኢሳያስ አፈወርቂ ስልጣን ላይ አደጋ የደቀነ ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰለሞን ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በሄደባቸው ቦታዎች ባይለፈልፍ እና ታማኝ መስሎ ስራውን ቢቀጥል ኖሮ ሻዕቢያዎች “ከስልጣን ተወግዶ እንኳ ሞራሉ ያልተነካ፤ ለስልጣን የማይስገበገብ ትክክለኛው የህዝብ ልጅ” በማለት በአንድ ቦታ ላይ ይሸጉጡት እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ ይሁንና ሰለሞን እንደ ጓዶቹ ብልህ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እዚያው “ሀለዋ ሰውራ” ውስጥ ተደራራቢ ስቃይ አይቶ፣ በቅማልና በትኋን ከተበላ በኋላ የመቀበሪያ ጉድጓዱን ራሱ ቆፍሮ በጥይት ተሰናብቷል (በየማናዊ ንቅናቄ ሰበብ የተያዙ ታጋዮች ከርሱ ቀደም ብለው በ1980 ነው የተረሸኑት፡፡ ሀይሌ ጀብሃም ከነርሱ ጋር ነበር የተገደለው)፡፡ በእስከ አሁኑ ትረካዬ እንዳያችሁት “ሀለዋ ሰውራ” የሚል ስም ደጋግሜአለሁ፡፡ በዚህ ስም የሚጠራው በሻዕቢያ ውስጥ እጅግ የሚፈራ ተቋም ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ብዙ ያልተጻፈለት ተቋም ምን ይመስላል? ወደፊት እናየዋለን፡፡ ሰላም!! አፈንዲ ሙተቂ ህዳር 10/ 2006 (ይቀጥላል) ምንጮች 1. Dawit Wolde-Giorgis, “Red Tears”: Famine, War and Revolution in Ethiopia, Red Sea Press, New York 1989 2. David Lamb, “Evil Days: Thirty Years of War and Famine in Ethiopia (1961-1991), Africa Watch Group, New York, 1991 3. Paul B. Henze, “Eritrea’s War”, Shama Books, Addis Ababa, 2002 4. ተሰፋሚካኤል ጆርጆ፤ የምጽዋ ስፖዚየም፣ ጥር 1974፣ ገጽ 60 (ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf) 5. ጌታቸው ሀይሉ፡ “ቀያይ ተራሮች”፣ አዲስ አበባ፣ 1993 6. ክፍሉ ታደሰ፣ “ያ ትውልድ”፣ ቅጽ አንድ፣ ኢንዲፔንደንት አሳታሚዎች፣ 1986 7. ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፣ አይ ምጽዋ፣ አዲስ አበባ፤ 1997 8. ጌታቸው የሮም፣ ፍረጅ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ 1994 9. ልዩ ልዩ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች እና ዌብሳይቶች የተገኙ ጽሑፎች *****
Posted on: Tue, 19 Nov 2013 13:48:32 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015