ኩረጃ፦ ከአፍጋኒስታን ለሐብሽስታን - TopicsExpress



          

ኩረጃ፦ ከአፍጋኒስታን ለሐብሽስታን (የሁለት ሙሳዒዲኖች ወግ) ቦታው አፍጋኒስታን ከሚገኝ አንድ ማስልጠኛ ካምፕ ነው። በካምፑ ውስጥ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ ጢማም “ታጋዮች” ልዩ ልዩ ስልጠና ሲወስዱ ሰንብተዋል። ስልጠናቸውን ካጠናቀቁት መካከል የተወሰኑትን ወደ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ የመን፣ ግብጽ፣ ሊብያ፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ምስራቅ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ ተልእኮ አስይዞ ለማሰማራት ምልመላ እየተካሄደ ነበር። ሰልጣኞቹን ለልዩ ተልእኮ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አንድ ስመጥር ምሁር ከሳውዲ መጥቷል። ይህ ምሁር ተመርጠው ለቀረቡለት ምልምሎች ሊፈትን በተዘጋጀለት ቢሮ ሲገባም የብዙ ሀገር ዜጎች መልኮች ያሏቸው ምልምሎች አንድ በአንድ እንድ ወደ ቢሮው ገብተው ሊፈተኑ ተራ ያዙ። ወረፋ ከሚጠብቁት ምልምሎችም ውስጥ ሁለት ሀበሾች ይገኙበታል፤ አል‐ ኑስራዊ አቡበከር አል‐ሓቢሺ እና አብዱል‐ለጢፍ አል‐ሓቢሺ! አል‐ኑስራዊ አቡበከር የቀድሞ መጠርያ ስሙ አበጋዝ ሙሔ ሲሆን አብዱል‐ለጢፍ ደግሞ የቀድሞ ስሙ ዲያቆን ስጦታው ሽብሩ ነበር። ሁለቱም ሀበሾች አፍጋኒስታን ሂደው ስማቸውን የቀየሩት ስለጠናው የአረብኛ የትግል ስም እንዲኖራቸው የግድ ስለሚል ነው። ይሁን እንጂ በካምፑ የነበሩ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞችና አልፎ አልፎ ካምፑን የሚጎበኙ እንግዶች ሁለቱን ሀበሾች በግርምትና በአድናቆት እየተመለከቱ “አል‐ሙሳዒዲን” ይሏቸው ነበር። ሁለቱ ሀበሾች ለየብቻቸው ሲሆኑ ግን አንዳቸው ላንዳቸው “ስጦታው” እና “አበጋዝ” እየተባባሉ ይጠራራሉ፤ ሌሎች ባጠገባቸው ካሉ ደግሞ የትግል ስማቸውን ይጠቀማሉ፤ ሲጠሯቸውም “ነዓም ኡስታዝ” ይላሉ። እናም ከሳውዲ የመጣው ፈታኝ ሲጠራቸው “ነዓም ኡስታዝ”(አቤት መምህር) ብለው ለመግባት ተራቸውን ይዘው በጉጉት እንደሚጠባበቁት ሁሉ የሳውዲውም ምሁር በተለይ የሁለቱን ሀበሾች ብቃት ለማየት ልዩ ትኩረት ሰጥቶበት ነበር። መጀመርያ አል‐ኑስራዊ አቡበከር ተጠራና ወደ ፈተና ክፍሉ ገባ። የሳውዲው ምሁር አል‐ኑስራዊን ከላይ እስታች በአድናቆት እያየ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ሰላምታ ሰጠና ቦታ አስያዘው። ስለግል ህይወቱ አንዳንድ ነገሮች ከጠየቀው በኋላ ቀጥታ ወደቃል ፈተናው ገባና ጥያቄውን አዥጎደጎደ። አል‐ኑስራዊም መጀመርያ ይገዳደረው የነበረው ሀበሻዊ ሀፍረት ለቀቀውና ጢሙን እያሻሸ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጠ። ጥያቄውና መልሱ የሚከተለውን ይመስል ነበር፦ ሳውዲው፦ “በእስልምናችን ላይ የተቀነባበረ ጥቃት የወጠነው ጽዮናዊነት መቼ ተመሰረተ?” አል‐ኑስራዊ፦ “በ1894” ሳውዲው፦ “ጽዮናዊነትን በመመከት ዝና ያተረፉ ሁለት አንጋፋ ፓርቲዎችን ስም ጥቀስ?” አል‐ኑስራዊ፦ “መጀመርያ ዋፍድ ፓርቲ አሁን ደግሞ አል‐ቃኢዳ” ሳውዲው፦ “ለዘመናችን የዓለም ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው በምንድነው ትላለህ?” አል‐ኑስራዊ፦ “በጂሃድ” ሳውዲው፦ “ጽዮናውያን እንደሚሉት በማርስ ህይወት አለ?” አል‐ኑስራዊ፦“ጽዮናውያን በሳይንስ ሳያረጋግጡ አለ ቢሉም በኪታቡ እንደተነገረኝ ከሆነ የለም” የሳውዲው ምሁር በአል‐ኑስራዊ፦ መልስ ተደስቶ አድናቆቱን በመግለጽ ከወንበሩ ብድግ ብሎ ሰለምታ በመስጠትና አብዱል‐ለጢፍ ለጥቆ እንዲገባ በመንገር አሰናበተው። ኮሪደር ላይ ደግሞ አብዱል‐ለጢፍ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። አብዱል‐ለጢፍ በአረብኛ ይሰጥ ስለነበረው ትምህርት አል‐ኑስራዊ ከኔ ይሻላል ብሎ ስለሚያምንም ድሮም አገርቤት እያለ እንደሚያደርገው በኩረጃ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከጀለ፤ እናም “የጥያቄዎቹን መልስ በቅደም ተከተል ንገረኝ” አለ። አል‐ኑስራዊም ሳያቅማማ መልሶቹን በቅደም ተከተል ለአብዱል‐ለጢፍ ዘርዝሮ ነገረው። አብዱል‐ለጢፍ መልሶቹን በቃሉ ሸምድዶ ጥያቄውቹን ሊጋፈጥ ተጀንኖ ወደ ፈተና ክፍሉ ገባ (ጀነን አባሉም ድሮ በዲያቆንነቱ ጊዜ ደጃሰላም ላይ ከነጥምጥሙ በክብር ይንጎማለል የነበረበትን ወቅት ይመስላል)። አብዱል‐ለጢፍ ወደክፍሉ እንደገባ የሳውዲው ምሁር በአድናቆትና በፈገግታ እየተመለከተ ሰላምታ ሰጥቶ ወንበር ላይ አስቀመጠው። ሳውዲው ወደ ጥያቄው ከመግባቱ በፊት ስለአብዱል ለጢፍ አንዳንድ ነገሮች ማወቅ ፈልጎ የግል ሁኔታዎቹን በተመለከተ ጥያቄዎችን አነሳለትና አብዱልለጢፍም መለሰለት፦ ሳውዲው፦ “መች ተወለድክ?” አብዱል‐ለጢፍ፦ “1894” ሳውዲው፦ “የአባትህ ስም ማነው?” አብዱል‐ለጢፍ፦“መጀመርያ ዋፍድ ፓርቲ አሁን ደግሞ አል‐ቃኢዳ” ሳውዲው፦“ህይወትህ በምን ትገለጻለች” አብዱል‐ለጢፍ፦“በጂሃድ” ሳውዲው፦“ለመሆኑ አእምሮ አለህ?” አብዱል‐ለጢፍ፦“ጽዮናውያን በሳይንስ ሳያረጋግጡ አለ ቢሉም በኪታቡ እንደተነገረኝ ከሆነ የለም” የአብዱል‐ለጢፍን መልስ እንደሰማ የሳውዲው ምሁር በጣም ተገረመ(እርግጥ አብዱል‐ለጢፍ ይህንን ቃለምልልስ ኋላ ለአልኑስራዊ ሲነግው ባንድ በኩል እያፈረ በሌላ በኩል ድሮ ኮሜድያን ልመንህና አለባቸው የሰሩት ቀልድ ትዝ ብሎት ፈገግ እያለ በድብልቅልቅ ስሜት ተውጦ ዝም ነበር ያለው። እንዲያውም ሳውዲው ተናድዶ አብዱል‐ለጢፍን “ነዓልዲነክ...” ምናምን ብሎ ይሰድበዋል ወይም ደግሞ ሳውዲው ጣልያንኛ ስለሚችል “ባፋንኩሎ...ቴስታ ዲ ካሶ...” ገለመሌ እያለ ይወርፈዋል ብሎ ጠብቆ ነበር)። ሳውዲው ግን “ላኢላላህ...አብዱል‐ለጢፍ ያሽኩራን....” ብሎ በጣም እየጮኸና ብዙ የምስጋና ቃላት በአረብኛ እያዥጎደጎደ ግጥም አድርጎ አቀፈው። ያውም አብዱል‐ለጢፍ ግራ እስኪገባው ድረስ። ሳውዲው በደስታ ስሜቱን መግለጽ ቀጠለ። “ሓቢሽስታን (ኢትዮጵያ) ውስጥ የሚያስፈልጉን እንዳንተ ያለ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። አንድ ሳይሆን ብዙ አብዱል‐ለጢፎች ያስፈልጉናል። ቅድም ስለህይወትህ ስጠይቅህ ‹በጅሃድ ትገለጻለች› ብለሃል አይደል?” አለው ለማረጋገጥ ትክ ብሎ እያየው። “አዎ” አለ አብዱል‐ለጢፍም የሳውዲውን ደስታ ይበልጥ ለማጠናከር። “አይዋ!...ተማም ዓል‐ሙሳዒዲን...ለጂሃድ የሚሆን ነገር በሙሉ ሀገሬ ታሟላልሃለች። ስለብሩ አታስብ የጂሃድ ፍላጎትህን ወደ ሓቢሽስታን ሂደህ ባስቸኳይ ፈጽመው። የማይነጥፈው ካዝናችንን ይዘህ ይሄ ልዩ አእምሮህ የተሸከመውን ፍላጎት ታሟላለህ። አልኑስራም ባንተ አመራር ስር ሁኖ ፍላጎትህን ሊያስፈጽም ይንቀሳቀስ፤ አብራችሁ በሓቢሽስታን ጂሃድ ፈጽሙ። ዝርዝር እቅዳችሁን በጋራ አውጡና በቅርቡ ስጡኝ። የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟላለሁ። ይቅናችሁ። በገንዘባችን ብቻ ሳይሆን በዱዓችንም ከጎናችሁ ነን” ብሎ ትከሻውን አሻሽቶ አብዱል‐ለጢፍን በፍቅር አሰናበተው። አብዱል‐ለጢፍ ከፈተና ክፍሉ እንደወጣ ኩረጃው እንደሰራለትና የልዩ አእምሮ ባለቤት መሆኑን እንዳረጋገጠለት በማወቁ ደስ አለው። የውስጡ ሙቀትም ጨመረ። በዙርያው ያለ ነገር ሁሉ ውብ ሁኖ ታየው። እነዚያ ኮሪደር ላይ ተኮልኩለው ወደፈተና ክፍሉ ለመግባት ተራ የሚጠብቁት እንደ መልአከሞት የሚያስፈራ ፊት ያላቸው ጢማም አፍጋኖችና “ግማታም አረቦች” እያለ በውስጡ ይጠላቸው የነበሩ ሰልጣኞች በሙሉ መላእክት መስለው ታዩት፤ “የህያው እግዚአብሔር መልእክተኞች” አላቸው በልቡ። ያቺ ከእግር ጥፍሯ እስከ ፊቷ በጥቁር ጨርቅ ተሸፋፍና እና ትከሻዋ ላይ ክላሽ አንግታ ተራ እምታስከብረው ሴትም “ኒንጃ” እያለ በውስጡ የቀለደባት ነገር ሁሉ ስህተት መሆኑ ታየውና “ይህቺ እኮ ራሷ እግዝእትነ ማርያም ማለት ናት” ብሎ በልቡ አመሰገናት፤ በአድናቆት፣ በፍቅርና በምስጋና ስሜት አይኖቹን ወደሷ እያንከራተተ ገረመማት። አብዱል‐ለጢፍ ከስሜቱ ድንገት የነቃው “ስጦታው እንዴት ነበር ፈተናው?” የሚል የሹክሹክታ ድምጽ ከጀርባው በኩል እንደሰማና አበጋዝ(አልኑስራዊ) ቀረብ ብሎ ትከሻውን ነካ ካደረገው በኋላ ነበር። ዞር ብሎም በደስታ አቀፈው። ፈተና ክፍሉ ውስጥ የሆነውን ሁሉ ያጫወተው ግን ከኮሪደሩ ራቅ ብለው በአማርኛ እንደልባቸው የሚያወሩበት ቦታ ካገኙ በኋላ ነበር። አበጋዝ ( አልኑስራዊ) የሳውዲውና የዲያቆን ስጦታው (አብዱል‐ለጢፍ) ምልልስ እንደሰማ መሳቅ፣ ማፈርና መደናገጥ የተቀላቀሉበት ስሜት ተሰማው፤ ሳውዲው የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንና “ዝርዝር እቅድ አውጡ” ማለቱ ግን ድብልቅልቅ ስሜቱን ሁሉ አስረሳውና በደስታ ተፍነከነከ። አብዱል ለጢፍ ግን አልኑስራዊ ላይ የተፈጠረውን ስሜት ላፍታም አላስተዋለም። ፊቱን ወደ አድማሱ አዙሮ ማሰብ ጀመረ። በምናቡም ወደ ድሮ እየተጓዘ ብሎም ወደ መጪው የተስፋ ጊዜም እያማተረ ብዙ አሰላሰለ። በአብዱልለጢፍ (ዲያቆን ስጦታው) አእምሮ ብዙ ነገሮች ብቅ ጥልቅ አሉ። “ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር” ሲታወጅ በብሄራዊ ውትድርና ታፍሶ የትግራይ ወንበዴዎችን ለመፋለም የዘመተበትን ወቅት፤ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” ብሎ ፎክሮ ገና ውግያ እንደገባ ሺሬ ላይ ተማርኮ በወያኔ እጅ በምርኮኝነት የወደቀበት ወቅት፤ በምርኮው ጊዜ ጥቂት ትምህርት ወስዶ ወደ ደርግ እንደተመለሰ፤ በሃኪም አስመስክሮ ዳግም በወታደርነት ከመሰለፍ ተገላግሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመዝግቦ መማር መጀመሩ፤ ከዚያም ‹ማርክሲዝም አያዋጣም› ብለው ፊታቸውን ወደ ሃይማኖት ያዞሩ አንድ የታሪክ ፕሮፌሰር ቢሯቸው ድረስ ጠርተውት አቡነ ጎርጎርዮስ ባስጀመሩት የሃይማኖት ስልጠና እንዲሳተፍ በክረምት ወቅት ወደ ዝዋይ ሀመረብርሃን ገዳም ልከውት በክህነት መሰልጠኑ፤ ወያኔ ወደመሃል ሀገር እየገፋ ሲመጣም ጓድ መንግስቱ ሃለማርያም የበጋው ትምህርት ተቋረጦ ሁሉም ተማሪ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስድ ሲያዝዙም ከዩኒቨርስቲ ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ ካምፕ መግባቱ፤ ብላቴ ላይ ደግሞ ዩኒቨርስቲው ውስጥ ፕሮፌሰሩ በህቡእ ያደራጇቸው “ታላላቅ ወንድሞች” በመባል የሚታወቁ ምሁራን “ወያኔንና ሰሜነኞችን ማቸነፍ የሚቻለው ከክላሽ ጎን ለጎን ጾምና ጸሎት ሲኖር ነው” ብለው እሱን ጨምሮ የተወሰኑትን ተማሪዎች “ማህበረ ቅዱሳን” በሚል ስም ማደራጀታቸው፤ የብላቴ ብላቴናዎች ተደራጅተው በጋራ ‹ቅዱሳን› በጋራ ቢባሉም ‹ቅዱስ ውግያ› ሳያደርጉ ወያኔ አዲስ አበባን መቆጣጠሩ...ወዘተ አስታወሰና በቁጭት ተንገበገበ። ወዲያውኑ የአሁኑ አጋጣሚ ድሮ የከሸፈውን ትግል በጂሃድ እንደሚክሰው ሲያስብ ስላለለፈው ሁሉ ውድቀት ተጽናና። “ግን እኮ” አለ በሃሳቡ፤ “ከብላቴ መልስ ያደረኩት ትግል ቀላል አይደለም” አለና ብዙ ነገሮችን አስታወሰ። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ የመደራጀትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲያውጅ እሱና ‹ቅዱሳን› ጓዶቹ በ“ታላላቅ ወንድሞች” አመራር በህቡእ እየታገዙ እድሉን እንዴት እንደተጠቀሙበት መለስ ብሎ በህሊናው ቃኘ። “የወያኔን መንግስት እስኪበቃው ጥምብእርኩሱን አውጥተነዋል” አለ በሃሳቡ። በተለያዩ ጋዜጦች የብእርስም እየተጠቀመ የወያኔን ባለስልጣናት ስም እንዴት እንዳበሻቀጠ፤ ‹የወያኔውን ጳጳስ› ለማዋረድ በፊያሜታ እና በአዲስ ነገር ጋዜጦች ላይ ያሳትማቸው የፈጠራ ጽሁፎች ትዝ አሉትና ፈገግ አለ። በየበዓላቱም “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች” የሚሉ ቲሸርቶች ለብሰው የሚሰለፉ ወጣቶችን በማደራጀት የነበረው ሚናም ታወሰው። በታላላቅ ወንድሞች እየታዘዘም ከተለያዩ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር የሚጣጣሙ ተልእኮዎች እየተሰጡት ሁሉንም እንዴት እንደተገበረ ትዝ አለውና ውስጡ ተከፋ፤ “ይሄ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ወያኔ እንደተዘባነነብን ይኑር” ሲል በቁጭት ተማረረ። “ግን ምንም አይደለም ይህ ሁሉ የማይሆን ነገር ያደረግነው እኮ ለኢትዮጵያ ስንል ነው” ብሎ ለመጽናናት ሲያስብ ቅድም ከሳውዲው ምሁር ጋር ሲነጋገር ኢትዮጵያን “ሓቢሽስታን” እያለ ይጠራ የነበረው ትዝ አለውና ትንሽ ጎረበጠው። “እርግጥ ብዙ ጋዜጠኞች፣ ገጣሚዎች፣ አርቲስቶችና ፖለቲከኞች ሓቢሽስታን ስንላቸው ሊከፋቸው ይችላል። ግን ‹ታላላቅ ወንድሞች› ወደ አፍጋኒስታን ሲልኩኝ ዓላማቸው ወያኔን ለመጣል የሚያስችል ስልጠና እንድወስድ ብለው ስለሆነ ይህንንም ስም አጽድቀው ሌሎችም እንዲቀበሉ ማድረግ አይከብዳቸውም” ብሎ ተረጋጋ። ቀጥሎ ወደ አእምሮው የመጣው ሀሳብ ግን ጥቂት ረበሸው። ብዙ ሰዎች በዲያቆንነት ስለሚያውቁት የአረብና የአፍጋን ድቅል ስም ይዞ ወደኢትዮጵያ ሲመጣ በጎሪጥ የሚያዩትና የሚሳለቁበት ወገኖች እልፍ አእላፍ ሁነው ከፊቱ ተደቀኑበት። “ለዚህም ግዴለም፤ ዘዴ አለው” አለ በሃሳቡ። ቀጠለናም “ትግሉን የሚመራው ኢንጅነሩ ነው ተብሎ በቪኦኤ ከተነገረ፣ ዓላማችንም የድሮውን ማስመለስ በተለይም ወያኔ የሰራቸውን ፎቆች አፍርሰን እርይበከንቱን ወደቀድሞ ገጿ መመለስ ነው ብለን በሸገር ኤፍኤም መግለጫ ከሰጠን እና “ታላላቅ ወንድሞች” በህቡእ ለሚያስተዳድሯቸው ጋዜጦችና የተቃውሞ ፓርቲዎች ቀድመው እንዲያሳምኑ ካደረግን በቂ ነው” ሲል ሊያጋጥም ይችላል ብሎ ላሰበው ችግር መፍትሄ በምናቡ አበጀ። የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ አምደኞች ጨምሮ ብዙ “ውድ የኢትዮጵያ(ኦ አሁን ሓቢሽስታን) ልጆች” ያላቸው ጸሃፍት የፌስቡክ ፕሮፋይላቸውን በአፍጋንና አረብ ድቅል ስም ለውጠው እየጻፉ በየድረገጹ የሚሰሩትን የፕሮፓጋንዳ ስራ አስታወሰና ስጋቱ ሁሉ ተወገደለት። በዚህ መካከል በስሜት ተውጦ “ዋናው ቆርጦ መነሳት ነው” ሲል ድምጹ ለአልኑስራዊ ተሰማ። አል‐ኑስራዊም አብዱል‐ለጢፍ ምን ያሰላስል እንደነበረ ለመገመት ሳይጨናነቅ በሰማው ቃል ብቻ ተነስቶ “ልክ ነህ ዋናው ቆርጦ መነሳት ነው አለ”። ቀጥሎም ጂሃዳችን በምን መፈክር እንጀምረው ተባባሉና ተወያዩ። በመጨረሻም ከአብዱልለጢፍ ልዩ አእምሮ በፈለቀው መፈክር ሊታገሉ ተስማሙ። እንዲህ ሲሉ፦ “ድምጻችን ይሰማ!” “ቆይ...ግን...ድምጻችን ስናሰማ ሀገራችንን ምን ብለን እንጥራት? ኢትዮጵያ ወይስ ሓቢሽስታን?” አለ አብዱል‐ለጢፍ ጥቂት የጎረበጠውን ነገር እየገለጸ። “ሓቢሽስታን ነው እንጂ እምንለው። አብደሃል እንዴ ታጋይ አብዱል ለጢፍ? እንደዛ ካልሆነኮ የሳውዲው ካዝና ጭራሽ አይከፈትም።” አለ አልኑስራዊም ነገሩን ሲያብራራ። “እውነትክን ነው። ሓቢሽስታን ነው ማለት ያለብን። የሚያሳዝነኝ ግን ኢትዮጵያን ለወያኔ መተዋችን ነው” ብሎ አብዱል ለጢፍ ከአልኑስራዊ ጋር ለሓብሽስታን ሊታገል ተስማማ። በዚያ ባፍጋኒስታን ሸለቆ ላይ ሁነውም ሁለቱም(አበጋዝና ስጦታው) ባንድነት “ጅሃድ አል ሓብሽስታን” ብለው በመጮህ ድምጻቸውን አሰሙ። በአፍጋን ምድር ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ነገሩ ሁሉ ሌላ ነው።
Posted on: Sun, 01 Sep 2013 19:26:30 +0000

Trending Topics



Recently Viewed Topics




© 2015